13/03/2026
የኢሚግሬሽን የዜግነት አገልግሎት ምዝገባ በከተማው መጀመሩ ከእንግልት አድኖናል ሲሉ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በወልድያ ከተማ ስራ መጀመሩ ካላስፈላጊ ወጭ እና ከእንግልት አድኖናል ሲሉ ፓስፖርት ሲቀበሉ ያገኘናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
የወልድያ ከተማ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በዛሬው ዕለት ፓስፖርት የመስጠት አገልግሎቱን ጀምሯል።
በፓስፖርት ርክክብ መርሃ ግብሩ ላይም የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ እና የአብክመ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ ተገኝተዋል።
ፓስፖርታቸውን ሲቀበሉ ካገኘናቸው መካከል ከመርሳ ከተማ የመጣው ራጉኤል አበራ እና ከሀራ ከተማ የመጣው ማህሙድ ማህመድ የኢሚግሬሽን የዜግነት ምዝገባ በወልድያ ከተማ መጀመሩ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደሌሎች ከተሞች የምናደርገውን ጉዞ አስቀርቷልናል ሲሉ ተናግረዋል።
ይኼም ካላስፈላጊ እንግልትና ወጭ እንዳዳናቸው ገልጸው አሻራ በሰጠን በአስራምስተኛ ቀን ፓስፖርታችን ተቀብለናል ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የወልድያ ከተማ ኗሪ የሆነችው ኢክራም ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሌሎች ከተሞች ይደረግ የነበረውን ጉዞ እና እስከ አራት ወር ድረስ ይሰጥ የነበረውን የቀጠሮ መራዘም እና እንግልት መቅረፍ በመቻሉ ደስተኛ ነኝ ብላለች።
ያለምንም ውጣውረድ አሻራ በሰጠሁ በአስራ አምስተኛ ቀኔ ፓስፖርቴን ተቀብያለሁ ስትልም ተናግራለች።
የቅርንጫፉ አስተባባሪ አቶ ሰይድ ሙሀመድ የቀጠሮ ምዝገባ መስጠት ከተጀመረበት ከየካቲት 16 ጀምሮ 1100 ዜጎችን መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም በተሰጣቸው ቀጠሮ መሠረትም የአምስት መቶ ሃምሳ ሦስት ዜጎች ፓስፖርት ታትሞ እንደመጣ ገልጸዋል።
ማንኛውንም አገልግሎት በጽ/ቤቱ ተገኝቶ መጠቀም እንደሚቻል የገልጹት አስተባባሪው የፓስፖርት ቀጠሮ እንናሰጣለን ከሚሉ አጭበርባሪዎችና ህገወጥ ደላላዎች ማህበረሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
👉ምንጭ:-የወልድያ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ነው
መጋቢት 03/2018 ዓ.ም