01/03/2026
የድሬዳዋ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት
ክቡራን የድሬዳዋና የመላው ሀገራችን ስፖርት ቤተሰቦች፤
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የዓለም አቀፍ ጨዋታዎቹን በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እንዲያደርግ ዕውቅናና ፈቃድ በማግኘታችን የተሰማኝን ከፍተኛ ደስታ በራሴና በድሬዳዋ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስም ለመግለጽ እወዳለሁ።
ይህ ታሪካዊ ስኬት ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን፣ በከፍተኛ ጥረትና ቁርጠኝነት የመጣ ውጤት ነው። በተለይም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ላደረጉት ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ለሰጡት የቅርብ ክትትልና ላሳዩት የስፖርት መሪነት ጥበብ በፌዴሬሽኑ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ። የእሳቸው ቁርጠኝነት ባይኖር ኖሮ ዛሬ ይህንን የምስራች ለመስማት ባልታደልን ነበር።
ይህ ስታዲየም መፈቀዱ ለከተማችን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚዋና ለገጽታ ግንባታውም ትልቅ ትርጉም አለው። የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪም እንደ ሁልጊዜው እንግዳ ተቀባይነቱንና ለብሔራዊ ቡድኑ ያለውን ፍቅር በተግባር እንደሚያሳይ እምነቴ ፅኑ ነው።
በመጨረሻም፣ ይህ ስኬት እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ የፌዴሬሽን አባላት፣ የሥራ ኃላፊዎችና ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ድሬዳዋ የሰላም፣ የፍቅርና የእግርኳስ ከተማ መሆኗን በዓለም አቀፍ መድረክ በድጋሚ የምታረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ስፖርታችንን ይባርክ!
ኮሚሽነር አለሙ መግራ
የድሬዳዋ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት