16/12/2025
የባህር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታድየም ዓለም ዓቀፍ ስታንዳርድ ጠብቆ መገንባቱ ለልምድ ልውውጥ አመቺ መሆኑ ተነገረ።
ታህሳስ 6/2018 ዓ.ም
ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንግዶች የባ/ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየምን ጎበኙ ።
የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃሳ አገኘሁ በጉብኝታቸው በሲዳማ ክልል በአዋሳ ከተማ የተጀመረውን ዓለም ዓቀፍ ስታድየም ግንባታ ለማስቀጠል የባህር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየምን መጎብኘት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረው ጉብኝታቸው ሰፊ ልምድና ተሞክሮን ለመቅሰም እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
የባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም በጣም ጥቃቅን የፊኒሽንግ ስራዎች ቢኖሩትም በካፍ እና ፊፋ ዓለም ዓቀፍ ስታንዳርድ የተገነባ እጅግ ውብ ስታድም ነው ሲሉም አቶ ጃሳ ተናግረዋል ።
የስፖርት ልማቱ ልፋትና ጥረትም ውጤታማ የሆኑ ሀገርን የሚያስጠሩ እንዲሁም የሚጠቅሙ ስፖርተኞችን ለማልማት ነውም ብለዋል።
ካሱ አሩሳ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው በጉብኝታቸው ወቅት በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን እንደቀሰሙ ተናግረው በሀገር አቀፍ ደረጃ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ በመንግስት በኩል በስፋት ታቅዶበት እየተሰራ እንደሆነ አስታውሰው ለዚህም የስፖርቱን ዘርፍ ልማት ማልማት ቀዳሚ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የአብክመ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋየ እንደተናገሩት ከሲዳማ ክልል የመጡት እንግዶች ጉዞ ዋና ዓላማ የአዋሳን ዓለም ዓቀፍ ስታድየም ለመገንባት የሚጠቅሙ ልምዶችን ለመቅሰም ከመሆኑም ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚጠቅም እንደሆነ ተናግረዋል ።
የባህር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታድየም መጠናቀቁ ከዛሬው የልምድ ልውውጥ ጀምሮ በርካታ የስፖርት ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ለባህር ዳር ከተማ ሰፊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን የሚያድል ተቋም እንደሆነ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል።