31/08/2026
🔴 ከቁጭት ወደ ተስፋ: የኢትዮጵያ ዳኝነት አዲስ መንገድ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኝነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እየተጻፈ ይገኛል። ለዓመታት በዳኞች ምልመላ፣ ልማትና እድገት ሥርዓት ላይ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመሠረት (grass root) የጀመረ ስትራቴጂያዊ ለውጥ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
የዚህ ትልቅ የለውጥ ጉዞ መነሻ እ.ኤ.አ በ2022 ዩጋንዳ ላይ በተካሄደው የሴካፋ የትምህርት ቤቶች ውድድር ወቅት የተከሰተ አጋጣሚ ነበር። በወቅቱ በስፍራው የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ኢትዮጵያ ለውድድሩ የላከቻቸው የፕሪምየር ሊግ ደረጃ ዳኞችን እንደነበር ተመለከቱ። ይህ አጋጣሚ ትልቅ ቁጭት በመፍጠሩ ተተኪዎች ላይ ተግባራዊ ሥራዎች እንዲሰሩ አሳሰቡ።
የብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸዋንግዛው ተባባል ይህን አጋጣሚ ሲያስታውሱ "ያ አጋጣሚ ለዛሬ ሥራችን መነሻ ሆኗል። የተተኪ ዳኞችን ልማት በስትራቴጂ መምራት እንዳለብን ያሳየን ነው" ይላሉ።
የዳኞች ኮሚቴው በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ አዲስ ስትራቴጂክ ፕላን ተቀርፆ የዳኛ ምንጮች ትምህርት ቤቶችና ወጣቶች እንዲሆኑ ሰፊ እንቅስቃሴ ተጀመረ። "ቀደም ሲል በታችኛው እርከን ላይ በሚያጫውቱ ዳኞች እና በፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች መካከል የተመጣጠነ የዕድሜ ስብጥር አለመኖር ለዳኝነት ማኔጅመንቱ አስቸጋሪ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።" ያሉት የዳኞች ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ይህንን ችግር ለመቅረፍ አዲስ የዳኝነት ሙያ መመርያ እንዲዘጋጅ መደረጉን ይገልፃሉ። መመርያው አዲስ ወደ ዳኝነት ሙያ የሚገቡ ግለሰቦች ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 22 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን በፌዴሬሽኑ ዝርዝር መስፈርት መሠረት ወደ መረጃ ቋት ገብተው ከሥልጠና ጀምሮ በቅርብ ክትትልና እገዛ ወደ ላይ የሚያድጉበት መስመር እነዲዘረጋ ተደርጓል።
እንደ አዲስ ፖሊሲ ከተቀመጡት ዋና ዋና አቅጣጫዎች መካከል የፌዴሬሽኑ የዕድሜ ውድድሮች በዕድሜ አቻ ወጣት ዳኞች እንዲመሩ ማድረግ መሆኑን አቶ ሸዋንግዛው ይናገራሉ። "ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ባሉ ወጣት ዳኞች ከ15 ዓመት በታች ውድድሮችን ይመራሉ። ከ17 ዓመት በታች ውድድሮችንም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ወይም በዛ የእድሜ አካባቢ ባሉ ዳኞች ይዳኛሉ። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የትምህርት ቤት ውድድሮች በተማሪ ዳኞች፣ የዩኒቨርሲቲ ውድድሮች ደግሞ በራሳቸው በዩኒቨርሲቲ ተማሪ ዳኞች እንዲከናወኑ ይደረጋል።"
በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና የዚሁ አዲስ ፖሊሲ ፍሬ ማሳያ ሆኗል። በውድድሩ ላይ የሚገኙት የጨዋታ አመራሮች ሙሉ በሙሉ በዚህ አዲስ የምልመላ መስፈርት ከተለያዩ አካባቢዎች የተመረጡ ታዳጊ ዳኞች ናቸው። ታዳጊዎቹ የጨዋታ አመራሮች እያሳዩ የሚገኙት የአመራርነት ብቃትም ከፍተኛ ተስፋ የሰጠ ሆኗል።
ዛሬ የተካሄዱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ በአካል ተገኝተው የታዳጊ ዳኞቹን እንቅስቅሴ የተመለከቱት የሴካፋ የዳኞች ኃላፊ ዓሊ አህመድ እና የፊፋ ኢንስትራክተር ሁሴን ጋቦኒ ለተጀመሩት ሥራዎች ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል። የሴካፋ የዳኞች ኃላፊ ዓሊ አህመድ በቦታው ተገኝተው ከተመለከቱ በኋላ "ዛሬ እዚህ በመገኘታችን በጣም ደስተኞች ነን። ይህ በእውነት ለኢትዮጵያ ዳኝነት በጣም ጥሩ ተስፋ ያለው ነው። ይህን በመመልከታችን ትልቅ ደስታን ሰጥቶናል። መሰል ፕሮጀክቶች ሁልጊዜ ልናያቸውና ልንደግፋቸው የምንፈልጋቸው ናቸው። ዳኞችን ሁልጊዜ ከመሰረቱ መገንባት አለብን" ብለዋል።
የዚህ አዲስ አቅጣጫ ውጤታማነት ቀስ በቀስ እየጎላ መጥቷል። ቀደም ሲል በሴካፋ የትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ የተላኩ ታዳጊ ዳኞች ዛሬ ላይ የፊፋ ኤሊት የጨዋታ አመራሮች ስልጠና ደረጃ እስከ መድረስ ችለዋል። ወጣቷ ረዳት ዳኛ ሀና ደመቀ በአንድ ዓመት ውስጥ የሴካፋ ትምህርት ቤቶች ውድድርን ከመምራት ተነስታ በዛሬው ዕለት በተጠናቀቀው የፊፋ ኤሊት የጨዋታ አመራሮች ስልጠና ላይ መካፈሏ የፕሮጀክቱን ትርጉም በሚገባ የሚያሳይ ሆኗል።
አቶ ሸዋንግዛው ተባባል በአዳማ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ እያጫወቱ ካሉ ወጣት ዳኞች መካከል የአንድ ወንድና አንድ የሴት ዳኛ በቀጣይ ለሚደረገው የሴካፋ የትምህርት ቤቶች ውድድር መላኩን ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የጀመራቸውን የስልጠና እንቅስቃሴዎች በመከተል ሌሎች ከተሞች እና ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ ተቀብለው እንዲተገብሩት ጥሪ አቅርበዋል።
ከቁጭት ተነስቶ በስትራቴጂ ታገዞ አዲስ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳኝነት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክሉ ብቁ፣ በእድሜ ለጋ እና በስነ-ምግባር የታነጹ ዳኞችን ለማፍራት ትልቅ መሰረት ጥሏል።
Ethiopian Football Federation
Amhara Football Referees
💥
✍️ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት እና ይቀላቀሉ።
✅ Telegram
https://t.me/Amhara21FootballReferees
✅ page
https://www.facebook.com/AmharaFootballReferees/
💥 Like 🔵 Share 🔴 Follow