22/06/2026
አርጀንቲና በሜሲ ግቦች ታግዛ ወደ ጥሎ ማለፍ ተሸጋገረች
**************
በ23ኛው ዓለም ዋንጫ ምድብ አስር 2ኛ ጨዋታዋን ያደረገችው አርጀንቲና፤ ኦሰትሪያን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
ቴክሳስ ላይ በተካሄደው ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና አግኝታው የነበረውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢያመክንም፤ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል።
እነዚህ ግቦች ለሊዮኔል ሜሲ በ23ኛው ዓለም ዋንጫ 5ኛ፣ አጠቃላይ በውድድሩ ተሳትፎ ታሪኩ ደግሞ 18ኛ ሆነው ተመዝግበዋል።
በዚህም ሜሲ በጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎዘ ተይዞ የነበረውን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን በእጁ ሲያስገባ፣ በሁለቱ ጨዋታ እርሱ ባስቆጠራቸው አምስት ግቦች 6 ነጥብ የሰበሰበችው አርጀንቲና ወደ ጥሎ ማለፉ መሸጋገሯን አረጋግጣለች።
ወደ አራተኛ የዓለም ሻምፒዮንነት የምታደርገውን ጉዞም አስምራለች።