11/05/2026
ከጥልቁ ጨለማ ወደ አውሮፓ ብርሃን
እግር ኳስ ከሜዳው አራት ማዕዘን በላይ ታሪክ የሚጻፍባት፣ የማይቻል የሚመስለው የሚቻልባት፣ ትናንት የወደቁ ዛሬ ከከዋክብት ጋር የሚደንሱባት ድንቅ ዓለም ናት።
በትናንትናው ዕለት በአውሮፓ እግር ኳስ ደማቅ ታሪክ ተፅፏል፤ የጣሊያኑ ኮሞ ከሲሪ ሲ አዘቅት ተነስቶ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአውሮፓ ታላላቅ መድረኮች ላይ ለመታየት በቅቷል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ኮሞ የሚለው ስም ሲነሳ የሚታወሰው ውብ ስም ያለው ሀይቅ እንጂ ጠንካራ የእግር ኳስ ክለብ አልነበረም።
ክለቡ በገንዘብ እጥረት ክስረት ተፈርዶበት፣ እስከ አራተኛው እና ሶስተኛው የጣሊያን ሊግ እርከን ወርዶ የነበረው ያን ያህል ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ነበር። ሆኖም ግን ትክክለኛ ራዕይ ከጠንካራ ስራ ጋር ሲጣመር ተአምር እንደሚሰራ ኮሞ ለዓለም አስመስክሯል።
ይህ ጉዞ፣ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ክለቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህ ስኬት ለደጋፊዎቹ ዝም ብሎ ድል አይደለም፤ ለዓመታት የከፈሉት መስዋዕትነት እና የማይጠፋ ተስፋ ውጤት እንጂ!
በሲሪ ሲ ጭቃ ውስጥ ሲንከባለል የነበረ ክለብ፣ ዛሬ በአውሮፓ ሰማይ ስር ስሙ እንዲጠራ ማድረግ የሚችለው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በስትራቴጂ እና ለእግር ኳስ ባለው ጥልቅ ፍቅር ነው።
አንዳንዴ እግር ኳስ ከሜዳው ተጫዋችነት ባለፈ ታላቅ አእምሮን ትፈልጋለች። ለኮሞ ደግሞ ያ አእምሮ ሴስክ ፋብሪጋዝ ነው።
ብዙዎች በታላላቅ ክለቦች ተጫውቶ ያበቃለት ኮከብ አድርገው ሲቆጥሩት፣ እርሱ ግን በጣሊያን ሀይቆች ዳርቻ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ መሰረቱን ጥሎ ነበር።
ፋብሪጋዝ ወደ ኮሞ የመጣው ተጫዋች ሆኖ ብቻ አልነበረም፤ የክለቡ ባለድርሻ በመሆን ጭምር ነው። ይህ ደግሞ በክለቡ ፕሮጀክት ላይ ያለውን ጥልቅ እምነት ያሳያል።
ክለቡ ከታችኛው ሊግ ሲነሳ 'የረጅም ጊዜ ራዕይ' እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የእርሱ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር።
ፋብሪጋዝ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ወዲያውኑ ወደ አሰልጣኝነት በመሸጋገር የቡድኑን የታክቲክ ቅርፅ ቀይሯል።
ቡድኑ በሜዳ ላይ የሚኖረውን የኳስ ቁጥጥር፣ የማጥቃት ፍጥነት እና የጨዋታ ብልሃት የእርሱን ዘመናዊ አስተሳሰብ የተከተለ እንዲሆን አድርጓል።
ፋብሪጋዝ በኮሞ መኖሩ ሌሎች ታዋቂ ተጫዋቾች እና ባለሀብቶች ወደ ክለቡ እንዲሳቡ ትልቅ ምክንያት ሆኗል።
ፋብሪጋዝ ባለበት ፕሮጀክት ውስጥ መሳተፍ' ለብዙዎች ትልቅ ክብር እና መተማመኛ ሆኖላቸዋል።
ባጭሩ ፋብሪጋዝ ለኮሞ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን፣ መሪ፣ ባለሀብት እና አሰልጣኝም ነበር።
ዛሬ ኮሞ የአውሮፓን አየር ሲተነፍስ፣ የዚህ ስፔናዊ ጥበበኛ አሻራ በጉልህ ይታያል። እግር ኳስን በሜዳ ላይ እንደመራው ሁሉ፣ ክለቡንም ወደ ታላቅነት መርቶታል።
South Radio and Television Agency