01/09/2026
ለ፡ ለሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮዎች
ለ፡ ለሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር ቦክስ ፌዴሬሽኖች
ጉዳዩ፡ የቦክስ ውድድሮች ዕውቅና፣ ፈቃድ፣ የሕክምናና የደህንነት መስፈርቶችን በጥብቅ ስለማስፈጸም
የተከበራችሁ የስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቦክስ ፌዴሬሽኖች፣
በአገራችን የቦክስ ስፖርት በአሁኑ ወቅት እያሳየ ባለው መነቃቃትና እድገት በርካታ የቦክስ ውድድሮችና ዝግጅቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መካሄዳቸው የሚያበረታታ ነው።
ይህ መነቃቃት ለቦክስ ስፖርት እድገት፣ ለወጣቶች ተሳትፎና ለአገራችን የስፖርት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ፌዴሬሽኑ ያምናል።
ሆኖም ግን፣ የፌዴሬሽኑን ቅድመ-ዕውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ፣ በቂ የሕክምና ዝግጅትና የደህንነት ሥርዓት ሳይሟላ የሚካሄዱ የቦክስ ውድድሮች መኖራቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እንዲህ ዓይነት ውድድሮች በስፖርተኞች ጤናና ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ሁሉም አካላት በተለየ ጥንቃቄ ሊከታተሏቸው ይገባል።
የቦክስ ስፖርት ከፍተኛ የአካል ግንኙነት ያለው ስፖርት በመሆኑ፣ የስፖርተኞችን ጤና፣ ደህንነትና ሕይወት በልዩ ጥንቃቄ መጠበቅ የግድ ነው። ስለሆነም ማንኛውም የቦክስ ውድድር ተገቢውን የቴክኒክ፣ የዳኝነት፣ የሕክምና፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጅትና የአጠቃላይ ደህንነት መስፈርቶች አሟልቶ መካሄድ አለበት።
በዚህ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ተያይዞ የላከው “የቦክስ ውድድሮች ዕውቅና፣ ፈቃድ፣ ሕክምናና የደህንነት መመሪያ” በዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር ሕጎችና መመሪያዎች፣ በዓለም አቀፍ ቦክስ ማህበር (IBA) እና በወርልድ ቦክሲንግ (World Boxing) የውድድር፣ የሕክምና፣ የዳኝነትና የስፖርተኞች ደህንነት መርሆዎች እንዲሁም ከአገራችን የስፖርት አስተዳደር ሥርዓት ጋር በማጣጣም የተዘጋጀ መመሪያ መሆኑን እንገልጻለን።
የመመሪያው ዋና ዓላማ የቦክስ ስፖርቱ እድገትና መነቃቃት በተገቢው የደህንነት ሥርዓት እንዲመራ፣ ስፖርተኞች ከሚከሰቱ የጤናና የአካል ጉዳቶች እንዲጠበቁ፣ ውድድሮችም በብቁ ዳኞችና ቴክኒክ ኦፊሴላዊያን፣ በተሟላ የሕክምና አገልግሎት፣ በተገቢ የሪንግ ደህንነትና በፌዴሬሽኑ ዕውቅና እንዲካሄዱ ማድረግ ነው።
ስለሆነም፣ ሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ የቦክስ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ቴክኒክ ኦፊሴላዊያን፣ ስፖርተኞች እንዲሁም የውድድር አዘጋጆች ተያይዞ የተላከውን መመሪያ በጥብቅ እንዲያስፈጽሙ እና በአካባቢያቸው የሚካሄዱ የቦክስ ውድድሮች የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላታቸውን በኃላፊነት እንዲከታተሉ እናሳስባለን።
በተለይም፦
የፌዴሬሽኑ ዕውቅናና ፈቃድ ሳይኖር፣
በቂ የሕክምና ማረጋገጫ ሳይኖር፣
ብቁ ዳኞችና ቴክኒክ ኦፊሴላዊያን ሳይኖሩ፣
ተሟላ የአደጋ ጊዜ ሕክምናና የደህንነት ዝግጅት ሳይኖር፣
የሚካሄዱ የቦክስ ውድድሮች ስፖርተኞችን ለከፍተኛ የጤናና የሕይወት አደጋ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ፣ እንዳይካሄዱ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ እናሳስባለን።
“የስፖርተኛ ሕይወትና ደህንነት ቀዳሚ ነው!”
የፌዴሬሽኑ የደህንነት መርህ
“No Medical Clearance – No Bout;
No Qualified Officials – No Competition
No Federation Approval – No Boxing Competition.
“የሕክምና ማረጋገጫ ከሌለ – ፍልሚያ የለም፤
ብቁ ዳኞችና ኦፊሴላዊያን ከሌሉ – ውድድር የለም፤
የፌዴሬሽኑ ዕውቅናና ፈቃድ ከሌለ – የቦክስ ውድድር የለም።
በመሆኑም፣ ይህ ደብዳቤና ተያይዞ የተላከው መመሪያ ከደረሳችሁ ቀን ጀምሮ በሁሉም የቦክስ ውድድሮችና የቦክስ ዝግጅቶች ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በሥራ ክልላችሁ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት በሙሉ እንዲደርስና በጥብቅ እንዲፈጸም እናሳስባለን።
ከሰላምታ ጋር!
ግልባጭ፦
ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር