03/09/2026
“የባሎንዶር ሽልማት ለፒኤስጂ ተጫዋቾች ሊሰጥ ይገባል” - ሉዊስ ኤንሪኬ
*****************
ከቀናት በፊት የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ዓለም ዋንጫን የመሰሉ ውድድሮችን ማሸነፍ የባሎንዶር የዓለም ኮከብነት ሽልማትን ለማግኘት ብቸኛ መስፈርት ሊሆን እንደማይገባ መናገራቸው ይታወሳል።
በዚህ ሳያበቁም በዓለም ዋንጫ ታሪክ 22 ግቦች በማስቆጠር የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የተሰኘው ኪሊያን ምባፔ ሽልማቱን ሊያገኝ ይገባል የሚል ሃሳብም ሰንዝረው ነበር።
ሉዊስ ኤንሪኬ ደግሞ ከዚህ የሞሪንሆ ሃሳብ ተቃራኒውን ሰንዝረዋል። አሰልጣኙ በግለሰብ ደረጃ እከሌ ማሸነፍ አለበት ብለው ስም ባይጠቅሱም፣ ተጫዋቾቻቸው በቀደመው የውድድር ዘመን በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድኖቻቸው ያስመዘገቧቸው ስኬቶች ለዚህ ሽልማት ብቁ የሚደርጋቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ከፒኤስጂ ጋር ያነሱትን ኡስማን ዴምቤሌ እና ክቪቻ ክቫራኬሊያን ጨምሮ፣ ከስፔን ጋር የዓለም ዋንጫን ያሳካውን ፋቢያን ሩዊዝን በመጥቀስ የቡድን አባሎቻቸውን ለሽልማቱ ተገቢ መሆን አብራርተዋል።
ኤንሪኬ “የሽልማቱ አሸናፊ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን አልያም ፒኤስጂ መሆኑ ግዴታ አይደለም” ለሚለው የጆዜ ሞሪንሆ ሃሳብ ምላሽ በሚመስል መልኩ ነው ይህን አስተያየት የሰነዘሩት።
“በዓለም ላይ በአሁን ሰዓት ከ12 ያላነሱ ታላላቅ ተጫዋቾች አሉ፤ ከነዛ ውስጥ ከአራት ያላነሱት ሪያል ማድሪድ ነው የሚገኙት” የሚለው የሞሪንሆ ሙግት ሌላኛው ነጥብ ነው።
70ኛው የባሎንዶር ሽልማት በህዳር ወር ለንደን ላይ ይካሄዳል።
በእድሪስ አህመድ