21/09/2026
⭕️“አንድ ተጨዋች ወቅታዊ ብቃቱ ነው የሚያስመርጠው ፣በጥርሱም በአፍንጫውም ጎል የሚያስቆጥር ከሆነ እመርጠዋለሁ “ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ
👇🏽
የኢትጲያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከዋሊያቹ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ አላማቸው ማሸነፍ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ።
በሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለሚስተናገደው የ 2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሱዳን እና ሴኔጋል ጋር ወሳኝ ጨዋታዎች የሚጠብቀው የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድንን ዝግጅት በተመለከተ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቡድናቸው የታክቲክ አቀራረብን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኙ "እንደ ብሔራዊ ቡድን አላማዬ ማሸነፍ ብቻ ነው። ብሔራዊ ቡድን ላይ በአምስት እና ስድስት ቀናት ባህል መመስረት አንችልም። ይሄንን ማድረግ የሚቻለው በክለብ ደረጃ ብቻ ነው" በማለት ተናግረዋል።
አሠልጣኙ አክለውም "አቅም ካለን ልናሸንፍ እችላለን። ግን ከኛ የተሻሉ ካሉ ልንሸነፍ እንችላለን። የኛ ዋነኛ አላማ እና ፍላጎት ግን ማሸነፍ ብቻ ነው። ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ በስምምነታችን ውስጥ ተካቷል "ሲሉ ተደምጠዋል።
40 ተጨዋቾችን ይዘን ዝግጅታችንን ለመጀመር አስበን ነበር ያሉት አሠልጣኙ ግን በክለቦች አህጉር አቀፍ ውድድሮች ምክንያት ከነሐሴ ስምንት ጀምሮ ዝግጅታችንን የጀመርነው 28 ተጨዋቾች ይዘን ነው ብለዋል።
ዋሊያዎቹ በዝግጅታቸው መጀመሪያ ያደረጉት የአካል ብቃት አሠልጣኝ በማምጣት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ ጥረት መደረጉን አሠልጣኙ ያነሱ ሲሆን በቆይታቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና የወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል።
አሠልጣኙ አሁን ላይ 23 ተጨዋቾች እንዳሏቸው ገልፀው የወዳጅነት ጨዋታዎችን ተመርኩዘው ተጨዋቾችን ሲቀንሱ ወቅታዊ ብቃትን በመመልከት ተጨማሪ ተጨዋቾችን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል እንደቻሉ አሳውቀዋል።
በዚህም መሰረት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ካርሎስ ዳምጠው እና በረከት ሳሙኤል፣ እንዲሁም ከሲዳማ ቡና ያሬድ ባየህ፣ አቤል ያለው፣ ቢንያም በላይ፣ መስፍን ታፈሰ እና ብርሃኑ በቀለ ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምዳቸውን በሚገባ አጠናቅቀዋል።
በተጨማሪም ስለ ካርሎስ ዳምጠው ሊጉ ላይ ጥሩ ብቃት እያሳየ አልመረጡትም አሁን ሀሳቦትን ቀይረው በምን ኳሊቲ አይተው መረጡት ለሚለው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሲመልሱ “የአንድ ተጨዋች የሚያስመርጠው በወቅታዊ ብቃቱ ነው ፣በጥርሱም በአፍንጫውም ጎል የሚያስቆጥር ከሆነ እመርጠዋለሁ “ ብለዋል
ከመጀመሪያ ተጋጣሚያቸው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን አጨዋወት ጋር በተያያዘ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኙ ካየናቸው ነገር አንፃር የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በክንፍ የሚጫወት ፣ ተሻጋሪ ኳሶችን የሚያበዛ ፣ ከራሱ ሜዳ በፍጥነት ለመውጣት የሚሞክር ቡድን ነው ግን አሁን ላይ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል በማለት መልሰዋል።
የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር በጁባ ሲያደርግ ሁለተኛውን ጨዋታ ከሴኔጋል ጋር ባህርዳር ላይ የሚያከናውን ይሆናል።
በመጨረሻም ዋና አሰልጣኙ የቡድናቸውን ዋነኛ ግብ ሲያብራሩ፣ ተጫዋቾችን በሚገባ በማቀናጀት ጠንካራና ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን በመገንባት ሀገሪቱን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አክለውም፣ “የምንሰራው ውጤት ለማምጣት ነው፤ የተሰጠንን የህዝብ አደራ በሜዳ ላይ በድል ለመወጣት ሙሉ ዝግጅት አድርገናል” ሲሉ ለጨዋታው ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።