05/01/2026
☯የማንነት እውነት
✍ደምስ ሰይፉ
“You’ll never know who you are unless you shed who you pretend to be. ” ― Vironika Tugaleva
⚡️በዙሪያችን ያለው ደመና በውስጣችን ያለውን ጸሐይ ከልሎታል… የየዕለታችን አመድ የመነሻችንን ፍም አዳፍኖታል… የአስተዳደጋችን ቅኝት የዕይታ አድማሳችንን ኮድኩዶታል፣ የአስተምሯችን ስሪት፣ የየቤተእምነታችን መሰረት፣ የአካባቢ፣ የሃገር፣ የሚዲያና የአብሮ ውሎ ሸንጓችን ጨለማ የማንነታችንን ግዝፈት ውጦታል… ትልቁን ምስል ለማየት ስለተሳነን ባየነው ልክ ራሳችንን ሰርተናል… በምልዓት ማየት ስላልጀመርን ለሽንቁር ማንነት ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል… ነባሩን ዘዬ ስላልፈተሽን አዲስ መንገድ ማየት አቅቶናል… የነገሩንን ስላመንን የሆነውን መጠየቅ ትተናል… አይቻልም ስላሉን አለመደፈሩን ተቀብለናል… እናም ዛሬ ራስዳሽኑ ማንነት በኮረት ጥላ ውስጥ ተጨልሟል…
⚜የማንነትን ጉዳይ… እንደየ ጥናት መስኩ ሃቲት፣ እንደየ መንግስታቱ ውልደት፣ እንደየ ማሕበረሰቡ ነባር ትውፊት፣ እንደየ ሐይማኖታቱ መፃሕፍት እንጂ እንደ ጥልቁ ማንነታችን ምንነት ለመተንተን ሞክረን አናውቅም… ለኛ ማንነት ማለት ብዙዎች የሚያቀነቅኑት ምንነት ነው – ከየልባችን የምንመክረው ዘላለማዊ ወግ አይደለም… ማንነት ለኛ ከመሰሎቻችን የተዋስነው የአደራ ዕቃ ነው – በነፍሳችን ሹክሹክታ ስምረት የሚሰራ ሁሉአዊ መልክ አይደለም… ማንነት ለኛ ከመሆን በኋላ በሆነ ሁነት ውስጥ የሚቀነበብ ወቅታዊ ነው – ከመሆን በፊት በነበረ፣ ባለና በሚኖር ምንጭ ላይ የቆመ ዘላለማዊ አይደለም…
🔆የልኬታችንን ምልዓተ ዓለምነት እንዳናይ አዚም ያደረገብን ማነው?… የምንጫችንን አልፋ እንዳናውቅ ነገር የሰራብን ማነው?… ከጥልቅነታችን የመሰረት ወለል የነቀለን ማነው?… በአንድነት አውድማችን ላይ እልፍነትን ያበራየው ማነው?… በስክነት ጉባኤያችን ውስጥ ጩኸት የዶለው ማነው?… እውነትን ከምናይበት ማማ ላይ ጽልመት የጋረደብን ማነው?…
⚜‘አንተ ማነህ?’ ላለን ሁሉ ማንነት ያልሆነ ማንነት ስንነግር ቆይተናል… ስማችን ያልሆነ ስም፣ ሃገር ያልሆነ ሃገር፣ ቀለም ያልሆነ ቀለም፣ ልክን የማይገልጽ ልኬት፣ ተናጥሎን የሚሰብክ ማንነት፣ ብስለትን የማይገልጽ ዕድሜ፣ ምንምነትን የሚያረቅ ታሪክ፣ … ወዘተ… በቀቀናዊ ኑረት…
⚡️ከመሆን በፊት የሆንከው መሆን ዘላለማዊ፣ ከመሆን በኋላ የሆንከው ሁነት ጊዜያዊ ነው… ዜግነትህ፣ ብሔርህ፣ የትምህርት ደረጃህ፣ ስራህ፣ መደብህ፣ የትውልድ ቦታህ፣ ቤተሰብህ፣ ሐይማኖትህ… ማናቸውም በ ‘እኔ’ ና ‘የኔ’ ቁናነት የሚሰፈሩ ነገሮችህ ማንነትህ አይደሉም… የትኛውም፣ ከእስከ አልባው ሕዋ በተናጥሎ የሚያስቀምጥህ ሃሳባዊውም ሆነ ቁሳዊ ምንትስ ማንነትህ አይደለም… ያንተ ማንነት የሌላውም ማንነት ነው… የእኔ፣ የእርሱ፣ የእነርሱ የሚባል ማንነት የለም… ማንነት አንድና ዘላለማዊ ነው… ዘላለማዊ ማንነት ስላለህ ዘላለምህ ውስጥ ሞት እንኳ የለም…
🔑 በ’እኔታ’ እና ‘አንተታ’ መገለጥ /Subjective manifestation/ ውስጥ እንመላለስ እንጂ የምንጫችን አንድነት /Oneness/ የሁለንተናችን አንድነት ነው… ይህም በሰው፣ በእንስሳ፣ በተክል፣ በፕላኔት፣ በጠፈር፣ በሕዋ… በሚታየውና በማይታየው ዓለም ውስጥ ባሉ መገለጦች ውስጥ ሁሉ ያለ አንድነት ነው… ሕብረት፣ ጋርዮሽ፣ ጥምረት፣ ሕብራዊነት፣ ትብብር አይደለም አነድ-ነት ነው… አንድ ላይ መሆን አይደለም አንድ ብቻ መሆን ነው… Self ውስጥ ቁጥር የለም… በቃ ‘መሆን’ Being ብቻ ነው ያለው…
💫ራማና ማሀርሺ እንደነገረን “The Self is beyond duality. If there is one there will also be two. Without one there are no other numbers. The truth is neither one nor two. It is as it is.”
🔆ማንነት አለኝ የምትለው አይደለም – የሆንከው እራሱ ነው… Possession በማንነት ውስጥ ቦታ የለውም… አንተነትህ ከማንነትህ የተነጠለ አይደለም – ማንነትህ ነው አነተነትህ… ማንነትህ ቅርጽ፣ ቀለም፣ መስፈሪያ፣ ድንበር አልያም ጠገግ የለውም – በሁሉ ያለ፣ በሁሉም የሚኖር ነው…
💫“All that we have to do is to give up identifying the Self with the body, with forms and limits, and then we shall know ourselves as the Self that we always are.” Ramana Maharshi
⚜አንተ ውስጥ ‘ሌላው’ አለ – ‘ሌላው’ ውስጥም አንተ አለህ… “Quantum Physics reveals thus reveals a basic oneness of the universe” – Erwin Schrödinger
💫 አንስታይን በበኩሉ ይህን ይላል … “A human being is part of the whole, called by us ‘Universe’; a part limited in time and space. He experiences himself, his thoughts and feelings as something separated from the rest—a kind of optical delusion of his consciousness. This delusion is a kind of prison for us, restricting us to our personal desires and to affection for a few persons nearest us. Our task must be to free ourselves from this prison.”- Albert Einstein
🔆ስለማንነትህ እንዲገባህ ማንንም አትጠይቅ… የማንነትህን ልኬት በሌሎች ግንዛቤ ውስጥም አትሻ… ከራስህ ጋር አውጋ! ወደውስጥህ ተመልከት…
⚡️ከውጭ የምታየው ሁሉ የውስጥያህ ነጸብራቅ ነው… አንተ ሕዋ ውስጥ ሳይሆን ሕዋው ነው አንተ ውስጥ ያለው እንደማለት…
💫“You are not IN the universe; you ARE the universe, an intrinsic part of it. Ultimately you are not a person, but a focal point where the universe is becoming conscious of itself. What an amazing miracle.” ― Eckhart Tolle, ‘A New Earth’
🔆ነፍስህ እስካላዜመችው ማንነት አይገባም… ከአዕምሮ ባርነት እስካልተላቀቅህ መሆን አይገለጽም… ወደ ውስጥ እስካልዘለቅህ ከራስህ ጋር አትገናኝም
🔑ልብህን ጠይቅ ይመለስልሃል!! የማንኛውም ጥያቄህ መልስ ማንነትህ ውስጥ አለ… ማንነትህን የማወቅህ ቅጽበት ውስጥ ደግሞ ደስታ – ዘላለማዊ ደስታ… እ-ፎ-ይ-ታ!!!
መልካም አሁን
⚜🔑⚜🔑⚜🔑⚜🔑⚜
ውብ ምሽት❤