29/05/2026
የጨወታ ቀን
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አርባ ሁለት ነጥቦችን በመሰብሰብ አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ንግድ ባንኮች ደረጃቸውን ለማሻሻል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይፋለማሉ። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፎ በሁለት ሽንፈት እና በሁለት አቻ የተለያየው ቡድኑ በተለይም ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የነበረ ቢሆንም በቀጣይ ጨዋታ በመድን ተሽንፏል። 32ኛው ሳምንት ላይ እንዲሁ ሸገር ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል መመለስ የቻለ ቢሆንም ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ስለተጋራ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ባለመቀመጡ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ መግባት ይኖርበታል።
አርባ ስድስት ነጥቦችን ሰብስበው አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ መሪዎች ይበልጥ ለመጠጋት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈ ሲሆን ተደጋጋሚ ሽንፈቶችንም በማስተናገድ ሳይጠበቅ ከዋንጫ ፉክክር እየወጣ ይገኛል። ፋሲል ከነማን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የነበረው ቡድኑ በወልዋሎ ተሸንፎ የአሸናፊነት መንፈሱን ያጣ ሲሆን በ33ኛው ጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋርም ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ግብ ማስቆጠር የተሳነው ቡድኑ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ መቆየት የሚፈልግ ከሆነ የፊት መስመሩን አጠናክሮ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይለዋል። ሆኖም ግን ተጋጣሚው ያለበት ደረጃም አስጊ ከመሆኑ አንፃር ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቡድኖች በሊጉ ደረጃ 17 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንከሰ 4 ጨዋታወችን ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5 ጨዋታ ማሸነፍ ሲችል ስምንት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው 39 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ባንክ 20 ግቦችን ኤሌክትሪክ ደግሞ 19 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያጣው ተጫዋች የለም። ኢትዮ ኤሌክትሪክም በተመሳሳይ በጉዳት ሆነ በቅጣት ነፃ ሆኖ የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋል።