17/01/2023
ወዳጆች እሁድ ስለምትጎበኙት ስፍራ ያለችኝን ጥቂት ግንዛቤ ካነበብኩት ተነስቼ ላካፍላችሁ።
ሱባ መናገሻ ጥብቅ ደን በአፍሪካ ቀዳሚው ፓርክ።
Suba Forest the oldest park in Africa.
ከ9,000 ሔክታር በላይ በሆነ መሬት የተንጣለለው ሱባ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታሪካዊ ፓርኮች አንዱ ሲሆን፣ በብዝሀ ሕይወት ከበለፀጉ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ በአፍሪካ ካሉ ፓርኮች ዕድሜ ጠገቡ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ ፓርኩ የተመሠረተው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ
ንግሥና ወቅት ነበር፡፡ ንጉሡ በወቅቱ ባዶ የነበረውን አካባቢ በዕፅዋት የሞሉት ወፍ ዋሻ ከተባለ ስፍራ ባስመጧቸው የዕፅዋት ዝርያዎች ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ1900 ዓ.ም. የጥብቅ ደን አዋጅ ባስነገሩበት ጊዜ በአዋጁ ከተካተቱ ውስጥ ይኸው ፓርክ አንዱ ነው፡፡ በአገሪቱ ግንባር ቀደም የሚባለው የችግኝ ጣቢያ የተቋቋመው በፓርኩ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የስልጣን ዘመን የተተከለው ሱክያ (አይረን ውድ) የተሰኘ ዛፍ ሱባን ከሌሎች ፓርኮች ልዩ ያደርገዋል፡፡
ዛፉ ፍሬ የሚሰጠው በ70 ዓመቱ ሲሆን፣ ለንጉሡ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል ከተበረከቱ ስጦታዎች አንዱ ነበር፡፡
በፓርኩ 500 ዓመት የሆነው (በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተተከለ) የፅድ ዛፍ ይገኛል፡፡ በፓርኩ ታሪክ አይረሴ ከሆኑት በ1892 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የገባው የእንጨት መሰነጠቂያ ይነሳል፡፡ በእንፋሎት ኃይል የሚሠራው ማሽኑ የተተከለው፣ ለመኳንንት የሚሆኑ ቤቶችን ለማዘጋጀት የሚውሉ እንጨቶች እንዲሰነጠቁበት ታልሞ ነበር፡፡ ማሽኑ ከተተከለ በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል ወደ 1,600 ሔክታር የሸፈኑ ዕፅዋት ተቆርጠዋል፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ደግሞ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ 3,500 ሔክታር የሚሆን ደን እንደተጨፈጨፈ ይናገራል፡፡ እንጨቱን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝም የባቡር ሐዲድ ተተክሏል፡፡
በወቅቱ ደኑ የደረሰበት ጭፍጨፋ በፓርኩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እንጨት መሰንጠቂያው በፓርኩ ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ቢጥልም፣ በታሪካዊነቱ ለጐብኚዎች ዕይታ ይቀርባል፡፡
ፓርኩ የሚገኝበት አካባቢ (ማለትም በአቅራቢያው ያሉት ሞገሌ፣ አደሬና ዳሞቻ የተባሉ ተራራዎችንም የያዘው) አካባቢ ወጨጫ ይባላል፡፡ በሆለታ አልያም በሰበታ መስመር ወደ ፓርኩ መሔድ የሚቻል ሲሆን፡ ፤ ፓርኩ ከጥቂት ዓመታት በፊት በፌደራል አስተዳደር ሥር መናገሻ ሱባ ፓርክ በሚል ይተዳደር ነበር፡፡ አሁን ሱባ ሰበታ ዲስትሪክት ፓርክ የሚል በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ሥር ይገኛል፡፡
ከባህር ወለል በላይ ከ2,200 እስከ 3,385 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው ፓርኩ 186 የአዕዋፋት ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ ግንደ ቆርቁር (አቢሲኒያን ዉድ ፓከር)፣ አቢሲኒያን ካት በርድ፣ ብላክ ሔርድ ሲስኪንና የሎ ፍሮንትድ ፓሮት የተባሉት ዝርያዎች አገር በቀል ናቸው፡፡ ፓርኩ ከ32 በላይ የሚሆኑ አጥቢዎች መኖሪያም ነው፡፡ 12 ከሚደርሱት ትናንሽ አጥቢ እንስሳቶች፣ ኋይት ሩትድ ራት (እግረ ነጭ ፍልፍል) እና 20 ከሆኑት ትልልቅ አጥቢዎች ደግሞ የምኒልክ ድኩላ አገር በቀል ናቸው፡፡
በፓርኩ ከ70 ዓይነት በላይ ዕፅዋት ያሉ ሲሆን፣ ጽድ፣ ወይራ፣ ጥቁር እንጨትና ዝግባ ይጠቀሳሉ፡፡ በፓርኩ ያሉ ዕፅዋት እርስ በእርስ ተሳስረው ስለሚታዩ ‹‹ጁኒፐር ኦልያ ቤልት›› የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፅዶቹ ሥር የበቀሉ ወይራዎች በፅዶቹ ላይ መጠምጠማቸው ይጠቀሳል፡፡
በፓርኩ አራት ካምፕ ሳይቶች (ጐብኚዎች እንደማረፊያ የሚጠቀሙባቸው) ቦታዎች አሉ፡፡