10/08/2025
✅የካፍ የአሰልጣኝነት ፈቃድ ደረጃዎች እና መስፈርቶች
#የአሰልጣኞችን ብቃት ለመለካት፣ ጥራት ለመጨመር፣ ደረጃ ለማረጋገጥ ሲል #ካፍ የተለያዩ የአሰልጣኝነት ሙያ ፈቃድ የባለሙያዎች ደረጃዎችን እና ሊሟሉ የሚገቡ መስፈርቶችን በማውጣት ከ2018 እ.ኤ.አ ጀምሮ አባል ፌደሬሽኖች በአስገዳጅነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤
በዚህ ፅሁፍ እስከ ድረስ ያሉትን የተለያዩ በጥልቀት የምንመረምር እና የምናብራራ ሲሆን በተጨማሪም እያንዳንዱን የፈቃድ ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ ብቃቶችን፣ ኃላፊነቶችን፣ ለማሰልጠን የተፈቀደላቸው የክለብ ቡድኖች ደረጃና የሊግ ደረጃ እንዲሁም ተያያዥ ነገሮችን በሰፊው የምናይ፣ የምንዳስስና የምናብራራ ይሆናል።
5. የካፍ ዲ ፈቃድ፡- የመነሻ/የመጀመሪያ ደረጃ (CAF D License: Foundation Level)
ወደፊት በአሰልጣኝነት ሙያ ለመዝለቅና እስከ ፕሮፌሽናልነት ደረጃ ድረስ ለመድረስ ለሚፈልጉ ሁሉ ይህ የካፍ ዲ ፈቃድ እንደ መነሻ፣ መሰረታዊና መጀመሪያ ደረጃ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤
ይህ የምስክር ወረቀት አሰልጣኞች ከታዳጊዎች፣ ከወጣቶች እና ከአማተር ተጫዋቾች ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን መሠረታዊ እውቀቶችን የሚያስጨብጥ ፣ ለአሰልጣኝነት ሙያ የሚያስፈልጉ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ እና ያላቸውን ክህሎቶች ለማዳበር የሚያዘጋጅ ነው።
ይህ የዲ ፈቃድ መሰረታዊ የአሰልጣኝነት መርሆዎችን ፣ የስልጠና ክፍለ ጊዜን እቅድ ማውጣት እና የጨዋታ ህግጋት የመጀመሪያ ምዕራፍን (an introduction to the laws of the game) በስልጠና ወቅት የሚሸፍናቸውና የሚዳሣቸው ይሆናል፡፡
የካፍ ዲ ፈቃድ ያላቸው አሰልጣኞች መሠረታዊ የታዳጊዎች ልማት ፕሮግራሞችን ለመምራት (grassroots development programs) ፣ በእድሜ እርከን የተከፋፈሉ የታዳጊና የወጣት ቡድኖችን ለማሰልጠን (U20, U17, U15) እና የመጀመሪያ ደረጃ አሰልጣኝነት ስልጠና ክፍለ ጊዜዎችን ለመከታተልና ለመውሰድ ብቁ ናቸው ።
4. የካፍ ሲ ፈቃድ፡ የልማትና የእድገት ደረጃ (CAF C License: Development Level)
በካፍ የአሰልጣኝነት የፈቃድ ደረጃዎች ቅደም-ተከተል ተዋረድን በመከተል ወደ ላይ ከፍ ለማድረግ ስንፈልግ ከካፍ ዲ ፈቃድ ቀጥሎ የምናገኘው የካፍ ሲ ፈቃድን ሲሆን፤
ይህ የካፍ ሲ ፈቃድ ከታዳጊዎች ከፍ ባሉ የዕድሜ ቡድኖች እና በውድድር ቦታዎቻቸው ላይ ያለውን የተጫዋቾች እድገት ላይ በዋናነት ትኩረት ይሰጣል።
ይህ የምስክር ወረቀት ጥልቀት ያለው የአሰልጣኝነት ዘዴዎችን ፣ የስልት ትንተናዎችን (ታክቲካዊ ትንታኔዎችን) እና የስፖርት ስነ-ልቦናን ያካተተ ስልጠናን ማጠናቀቅ የሚገልፅ የእውቅና ማረጋገጫ ነው።
የካፍ ሲ ፈቃድ ያላቸው አሰልጣኞች በአካዳሚ፣ በታዳጊ፣ በወጣት እና በአማተር ሊግ (ብሔራዊ ሊግ) ደረጃ የሚገኙ ቡድኖችን በዋና አሰልጣኝነት ማሰልጠንና መስራት ይችላሉ፤
የካፍ ሲ ፈቃድ ያላቸው አሰልጣኞች ተጫዋቾችን ከመሰረታዊ ክህሎቶቻቸው ወደ ላቁና ከፍ ወዳሉ ቴክኒኮች እንዲያሳድጉ እና በሊግ ደረጃ እንዲጫወቱ ለማድረግ ይሰራሉ፡፡
3. የካፍ ቢ ፈቃድ፡ የላቀ ደረጃ (CAF B License: Advanced Level)
የካፍ ቢ ፈቃድ ታቅዶ የተነደፈውና የተዘጋጀው የአሰልጣኝነት ፈቃድ ደረጃቸውን ለማሳደግና ወደ ከፍተኛ የሙያ ደረጃ መሸጋገር ለሚፈልጉ አሰልጣኞች የተዘጋጀ ሲሆን፤
ብዙ ጊዜ ፕሮፌሽናል እና ከፊል ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ለማሰልጠን፣ ለማስተዳደርና ብቁ ለማድረግ ያለመ የፈቃድ ደረጃ ነው ።
ይህ የምስክር ወረቀት የተራቀቁና የላቁ ታክቲካል ስልቶችን፣ የተጫዋቾች አስተዳደርን እና ጥልቀት ያለው የጨዋታ ትንተናን ያካተተ ስልጠናን ማጠናቀቅ የሚገልፅ የእውቅና ማረጋገጫ ነው።
የካፍ ቢ ፈቃድ ያላቸው አሰልጣኞች ፕሮፌሽናል የወጣት አካዳሚዎችን ፣ የተጠባባቂ ቡድኖችን፣ በሁለተኛ ደረጃ ሊጎች (ከፍተኛ ሊግ) ላይ የሚወዳደሩ ቡድኖችን ወይም ከፊል ፕሮፌሽናል ክለቦችን ለመምራትና ለማሰልጠን ብቁ ናቸው፤ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በረዳትነት ሊሳተፉ ይችላሉ ።
2. የካፍ ኤ ፈቃድ : የከፍተኛ ደረጃ ( CAF A License: Elite Level)
የካፍ ኤ ፈቃድ ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ደረጃ ሲሆን የላቀና ከፍተኛ የሆነ የቴክኒክ እና የታክቲክ ዕውቀትን መለኪያ በማድረግ የሚሰጥ የፈቃድ ደረጃ ነው።
የካፍ ኤ ፈቃድ ያላቸው አሰልጣኞች የፕሮፌሽናል ክለብ ዋና ቡድኖችን ማሰልጠን የሚችሉ ሲሆን ውስብስብ የሆኑ ስልቶችንና ስትራቴጂዎችን ነድፈው በከፍተኛ የውድድር ደረጃዎች ላይ የመምራት እና መመሪያ የመስጠት ብቃት፣ አቅምና እውቀት ያላቸው አሰልጣኞች ናቸው ።
ይህ የምስክር ወረቀት ብሔራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን እና በአፍሪካና በዓለም ከ23ና ከ20 ዓመት በታች የቻን ዋንጫ መድረኮች ላይ ለመምራት ወይም ፕሮፌሽናል ክለቦችን በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመምራት፣ ይዞ ለመቅረብና ለማሰልጠን በቅድመ ሁኔታ ለአሰልጣኞች የሚቀመጥ መስፈርት ነው ።
1. የካፍ ፕሮ ፈቃድ: የበቃ ፕሮፌሽናል/ባለሙያ ደረጃ (CAF Pro-License: Expert Level)
የአሰልጣኝነት ብቃቶች ቁንጮና ከፍተኛ ደረጃ የሆነው የካፍ ፕሮ ፈቃድ በጣም ልምድ ላላቸው እና በሙያቸው ውጤታማ ለሆኑ (ለተሳካላቸው) አሰልጣኞች የሚሰጥ የአሰልጣኝነት ፈቃድ ደረጃ ነው ።
የዚህ ፈቃድ ደረጃ ምስክር ወረቀት አሰልጣኞችን በእግር ኳስ ውስጥ በጣም አስፈላጊና በጣም አስቸጋሪ ለሆኑ ሚናዎች የሚያዘጋጅ እና እንደ አፍሪካ ዋንጫ (AFCON) ወይም የፊፋ የዓለም ዋንጫ ወይም የኦሎምፒክ ውድድሮች ባሉ ታላላቅ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ብሔራዊ ቡድኖችን ማሰልጠን እንደሚችሉ የሚገልፅ የእውቅና ማረጋገጫ።
የፕሮ ፈቃድ መርሃ ግብርና ስርአተ ትምህርት የላቀ ከፍተኛ የአሰልጣኝነት አሰለጣጠን ዘዴዎችን ፣ የአመራር ክህሎቶችን እና ከፍተኛ ልምድና ፕሮፋይል ያላቸው ተጫዋቾችን የማስተዳደር ችሎታን ያካተተ ስልጠና የሚሰጥበት የአሰልጣኝነት የፈቃድ ደረጃ የመጨረሻው ደረጃ ነው።
በ የካፍ የአሰልጣኝነት ፈቃድ የተለያዩ ደረጃዎችን ( እስከ ድረስ) እና መስፈርቶችን እንዲሁም ለእያንዳንዳንዱ ደረጃዎች የሚያስፈልጉና ሊሟሉ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ፣ ብቃቶችንና ኃላፊነቶችን በጥልቀት የምናይ የምንመረምር እና የምናብራራ ሲሆን፤
በተጨማሪ የካፍ አሰልጣኝነት ፈቃድ መስፈርቶችን በክለቦች የደረጃ ዓይነት፣ በውድድር ደረጃ እና በሚያስፈልገው የአሰልጣኝነት ፈቃድ ደረጃ ላይ በመመርኮዝና መሰረት አድርገን በመከፋፈል በዝርዝር የምናያቸውና የምንዳስሳቸው ይሆናል፡፡
ይቀጥላል .................
©️ Bereket Dereje Mekonnen
(FIFA Licenced Football Agent, Authorized FIFA Legal Portal Representative, CAS Legal Representative)